በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገቢ አሰባሰብን በማዘመን ወጪ ቆጣቢ የበጀት አጠቃቀም ስርዓትን መዘርጋት እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገቢ አሰባሰብን በማዘመን ወጪ ቆጣቢ የበጀት አጠቃቀም ስርዓትን መዘርጋት እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ

**************

(አሶሳ፣ ታህሳስ 24/2016 ዓ.ም) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገቢ አሰባሰብ ሂደትን በማዘመን ወጪ ቆጣቢ የበጀት አጠቃቀም ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን እና የፋይናንስ ቢሮ የ5 ወራት የእቅድ አፈፃፀም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚረጋገጠው ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ እና ለታለመለት ዓላማ ማዋል ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ሰርዓትን ከማዘመን ባለፈ ውስን የሆነውን የመንግስትና የህዝብ በጀት ለታመለት ዓላማ በማዋል የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የሚሰበሰበውን ገቢ ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ወጪ ቆጣቢ የሆነ ስርዓት በመዘርጋት እየተሠራ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ባለፉት አምስት ወራት ጥሩ የሚባል አፈፃፀም ቢኖሩም በቀጣይ ወራት ሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ወረዳዎች አቅማቸውን አሟጠው ገቢ ሊሰበስቡ እደሚገባቸውም አቶ አሻድሊ አሳስበዋል።

በክልሉ ገቢ የመሰብሰብ አቅም እያደገ ቢመጣም በገቢ አሰባሰብ እና አጠቃቀም ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መለሰ ኩዊ በተያዘዉ የ2016 የግብር ዘመን በአምስት ወር ብቻ 1 ቢሊዮን 493 ሚሊዮን 923 ሺህ 767 ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅሰው፣ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 1 ቢሊዮን 282 ሚሊዮን 776 ሺህ 484 በመሰብሰብ የእቅዱን 86 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት ዲቢሳ በበኩላቸው፣ ተቋማትና ወረዳዎች በዓመቱ የተፈቀደላቸውን በጀት አጣጥመው በመጠቀም የበጀት ብክነትን ሊከላከሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመድረኩም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የዞን፣ የከተማ አስተዳደር እና የወረዳ የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *