ዜናዎች

በክልሉ የዜጎች አካታች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተቋማት ቅንጅት ሊጠናከር እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ

በክልሉ የዜጎች አካታች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተቋማት ቅንጅት ሊጠናከር እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ፡፡

‎የክልሉ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከኩሶ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተቋማት አካቶ ትግበራ ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

‎የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በመድረኩ እንደተናገሩት፣ መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡

‎እንደሀገር የተጀመረውን ብልጽግና ለማረጋገጥ አካታች የሆነ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አቶ ጌታሁን፣ የዜጎችን አካታች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቋማት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‎የሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ሥራ መሥራት የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ተናግረው፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የበኩላቸውን ጥረት ሊያርጉ እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

‎የክልሉ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ይባስ፣ ቢሮው በበጀት ዓመቱ የሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች አካቶ ትግበራን ውጤታማ ለማድረግ የተሻለ ጥረት እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

‎ለተቋማት አካቶ ትግበራ ውጤታማነት የምዘና ስርዓት መዘጋጀቱን የገለጹት ወ/ሮ አለምነሽ፣ ባለድርሻ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

‎በክልሉ የኩሶ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ መሐሪ ታደለ፣ ኩሶ ኢንተርናሽናል በክልሉ በትምህርት፣ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ከመንግስት ዕቅዶች ጋር የተናበበ ፕሮጀክት በማዘጋጀት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡

‎ድርጅቱ በአቅም ግንባታ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በቁሳቁስ፣ በስነ ልቦና የጀመራቸውን ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

‎የስልጠናው ተሳታፊ አመራሮች በበኩላቸው፣ የሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሁሉም ድርሻ መሆኑን አንስተው፣ ቀደም ሲል የሚስተዋሉ የግንዛቤ እና የቅንጅታዊ ሥራ ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባ አንስተዋል፡፡