በክልሉ በማዕድን እና በግብርና ዘርፍ የሥራ ክህሎትን በማዳበር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው -አቶ አሻድሊ ሃሰን::

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማዕድን እና በግብርና ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን የሥራ ክህሎት ለማዳበር እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አመራሮችን ያካተተ ቡድን በክልሉ የሥራ እድሎችን በክህሎት መምራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የመስክ ጉብኝት ማድረግ ጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት ክልሉ በተለይ በግብርና፣ በማዕድን እና በእንስሳት ዘርፍ ያለውን እምቅ ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ባለፉት ዓመታት በርብርብ ሲሰራ ቆይቷል።

በእዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ሃይል ወደስራ በማስገባት የሚበረታታ ውጤት ማምጣት ተችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በስራውም የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም የህብረተሰቡን ኑሮ እየተለወጠ ከመምጣቱ ባሻገር ለኢኮኖሚውም አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

ይሁንና አሁንም በተለይ በግብርና እና በማዕድን ዘርፉ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሥራ ክህሎት የማሳደጉ ሥራ የተለያዩ አካላትን ድጋፍ ይጠይቃል ያሉት አቶ አሻድሊ፣ የክልሉ መንግስት ትኩረትም እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይ ተግባራዊ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ምርታማነትን በማሳደግ ህብረተሰቡ ዘላቂ በሆነ መንገድ ከድህነት እንዲላቀቅ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይ በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ያላቸውን የሰው ሃይል እና መሳሪያ በአግባቡ በመጠቀም የህብረተሰቡ የፈጠራ እና የክህሎት አቅም ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አቶ አሻድሊ አሳስበዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው የሚኒስቴሩ ልዑካን በክልሉ ለቀናት በሚኖራቸው ቆይታ የተፈጠሩ የሥራ እድሎች በክህሎት እየተመሩ መሆኑን በጥልቀት ይመለከታል ብለዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ክፍተቶችን በጋራ በመሙላት ምርታማነትን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሮ የጋራ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። በልዑኩ አባላት የመንግስት እና የግል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች፣ የወርቅ ማምረቻ እና የተለያዩ ኢንተርፕራዞችን የሥራ እንቅስቃሴ እንደሚጎበኝ ታውቋል።

One thought on “በክልሉ በማዕድን እና በግብርና ዘርፍ የሥራ ክህሎትን በማዳበር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው -አቶ አሻድሊ ሃሰን::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *