ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን የመልማት ቁጭታቸውን የተወጡበት ትልቅ የታሪክ አሻራ ነው

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን የመልማት ቁጭታቸውን የተወጡበት ትልቅ የታሪክ አሻራ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ’” የተሰኘ መጽሀፍ ዛሬ አስመርቋል፡፡

በመርሃ ግብሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራ አንዴሞ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡

“ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ” መፅሐፍ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከጽንሰት እስከ ውልደት የሀገር ኩራት የመሆኑን ፍፃሜውን ይዳስሳል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን የመልማት ቁጭታቸውን የተወጡበት ትልቅ የታሪክ አሻራ ነው፡፡

በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ በዚህ ዘመን ትውልድ ለፍፃሜ መብቃቱን በማንሳት፤ የተከፈለውን ዋጋ ለታሪክ መሰነድና መረጃዎችን አደራጅቶ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተሰነደው “ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ” መጽሐፍ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክት የተመረቀበት ብቻ ሳይሆን የትርክት ለውጥ የተደረገበት ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከጅማሬ እስከ ፍፃሜ ድረስ በተለያዩ ቋንቋዎች ዘገባዎችን ተደራሽ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፤ ግድቡን በተመለከተ የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተያየቶችን ስንመክት ቆይተናል ብለዋል፡፡

“ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ”’ መጽሐፍ የህዝቡን የዘመናት ቁጭት የሚዘክር፣ ተጋድሎን የሚያስታውስና የዘመኑ ትውልድ ለድል የበቃበትን መንገድ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከዓባይ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ማወቅ ለሚፈልግ ምላሽ የሚሰጥ እና ለጥናትና ምርምር ስራዎችም በግብአትነት የሚያገለግል መሆኑን አንስተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *