በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2018 የመስኖ እርሻ ሥራ ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2018 የመስኖ እርሻ ሥራ ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

‎‎የ2018 በጀት ዓመት የመስኖ እርሻ ልማት ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ “የመስኖ እርሻ አቅማችንን ለሕዝብ ኑሮ መሻሻል በተግባር” በሚል መሪ ቃል ዛሬ ተካሂዷል።

‎‎በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ መንግሥት ምርትና ምርታማነትን ለማሣደግ ግብርናውን በማዘመን ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

‎‎በተያዘው የመኸር ወቅት እየተከናወነ የሚገኘውን ተስፋ ሰጪ የግብርና ሥራ በመሥኖ ልማት ለማስቀጠል ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

‎‎በክልሉ ከክረምት እስከ በጋ ሊለማ የሚችለውን ሰፊ መሬት በማልማት የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑንም አቶ አሻድሊ አንስተዋል።

‎‎መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለመስኖ እርሻ ውጤታማነት የሚያግዙ የጀነሬተር እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ሲያደርግ መቆዬቱን ገልጸዋል።

‎‎ባለፉት ዓመታት የተገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በሙሉ አቅማቸው ወደሥራ ማስገባት ይገባል ያሉት አቶ አሻድሊ፣ ለመስኖ እርሻ ውጤታማነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

‎‎የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኻሊፋ በበኩላቸው፣ በተጠናቀቀው 2017 የመስኖ እርሻ ከ47 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በማልማት 11 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል።

‎‎በዘንድሮው የ2018 የመስኖ እርሻ ከ65 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት መታቀዱን ጠቅሰው፣ ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

‎‎በ2017 በጀት ዓመት ብቻ 13 አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ጠቁመው፣ ይህንን አቅም መጠቀም ይገባል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *