ተግባርና ሃላፊነት

የቢሮው ዝርዝር ዓላማዎች

1.ዜጎች በመንግሥት ቁልፍ አጃንዳዎች፣ አፈፃፀሞችና በወሳኝ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጠራ መረጃን በወቅቱ እንዲያገኙ በመረጃ አቅርቦት የተደራጀ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መስጠት፤

2.በዕውቀት፣ በክህሎትና አስተሳሰቡ የጎለበተ የዘርፉ የሰው ኃይል፣ በጠንካራ አደረጃጀትና አሠራር የተገነባ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዐቅም በቀጠይነት መፍጠር፤

3.በዲጂታል ቴክኖሎጂዎችንና ዘርፈ-ብዙ የሚዲያ አውታሮች በመጠቀም ሀገራዊ ጥቅሞችንና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት በማጎልበት፣ ኅብተረተሰቡ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲያገኝ በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት መካከል የተቀናጃና የተናበበ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማድረግ፤

4.ለመንግሥት የመረጃና የተግባቦት ሥርዓት ብቁ አመራር በመስጠት፣ ሕዝቡ በዋና ዋና ጉዳዮች ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጥርና የሀገሪቱ መልካም ገጽታና ተሰሚነት እንዲጎለብት ስትራቴጂካዊ አመራር መስጠት፤

የቢሮው ስልጣንና ተግባር

1.የክልሉ መንግስት ቃል አቀባይ እና ዋነኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን ይሰራል፤በክልላዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ የክልሉን አቋም ለህዝብ ይፋ ያደርጋል፤በየደረጃው ያለው የመረጃና የመረጃ ልውውጥ መዋቅር ለየተመደበበት የክልሉ አደረጃጀት በቃል አቀባይነት ኃላፊነቱን የሚወጣበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤

2.የክልሉን ስራዎች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ሁሉንም አይነት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ግብዓቶችን እና ውጤቶችን በብቃት፣ በጥራትና በስፋት በመጠቀም የመንግስት  ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ተደራሽ በማድረግ በህዝብና በመንግስት መካከል  የሁለትዮሽ ተግባቦት እንዲፈጠር ያደርጋል፤

3.የመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን መሰረት በማድረግ ማህበረሰቡን ተደራሽ የሚያደርጉ አጀንዳዎች በማዘጋጀት የተግባቦት ስራን ይሰራል፤

4.የመንግስትን ፖሊሲ፣አቋምና ዕቅድ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችሉና የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያሳድጉ ንቅናቄዎችን ይፈጥራል፤አፈጻጸማቸውን ይከታተላል፤ ለማህበረሰቡ ያሳውቃል፤ ወዘተ —–

5.ሀገራዊና ክልላዊ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን፣ሀገራዊና ክልላዊ መግባባትን፣የዴሞክራሲ ባህል መጎልበትን እንዲሁም ሁለንተናዊ እድገትን ማረጋገጥ እንዲቻል በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሚዲያዎችን ያስተባብራል፤ ከሀገር አቀፍና አለማቀፍ ሚዲያዎች ጋር በትብብር ይሰራል፤

6.በክልሉ መንግስት አስፈጻሚ ለሆኑ ሴክተር መ/ቤቶችና ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ዘርፎች ለስራዎቻቸው የሚሆኑ የአሰራር መርህ፣ ደረጃና ስርዓት በማውጣት እንዲተገበር ያደርጋል፤

7.በክልሉ ለሚገኙ ሴክተር መ/ቤቶች የህዝብ ግንኙነት ዘርፎች፣ ለዞን፣ ለከተማ አስተዳደር እና ለወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መዋቅሮች የሁለትዮሽ የተግባቦት ስራን ለማከናወን የሚያስችል አቅም ይገነባል፤

8.ከህዝብ ሰላምና ደህንነት ፣ ከታላላቅ ሀገራዊ እና ክልላዊ ክንውኖች ፣ ከተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ፣ ከህዝብ ንቅናቄ ሥራዎች ፣ ከግጭቶች ፣ ወዘተ ጋር በተያያዘ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ከሚመለከታቸው አካላት በዳሰሳ ጥናት እና በህዝብ አስተያየት ቅኝት መረጃ ይስበስባል ፣ ይተነትናል ፣ ድምዳሜዎችን ለሚመለከታቸው ያሳውቃል እንዳስፈላጊነቱ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል ፣ ለውጡን ይከታተላል ፤

9. በሀገራዊ እና በክልላዊ ጉዳዮች ላይ በመመስረት የተለያዩ  ዜናና ፕሮግራሞችን ያዘጋጃል፤ ይገመግማል ፤ ለክልልና ለሀገር አቀፍ ሚዲያዎች ይልካል፤ ተደራሽነታቸውን ይከታተላል፤

10.  የተለያዩ ኒው ሚዲያዎችን  በመጠቀም ተደራሽነታቸው ስፋት እንዲኖረው ያደርጋል፤ የመንግስትን እቅዶችና ተግባራትን ወደ ህዝብ ለማድረስ የሚረዱ ሀገራዊ እና ክልላዊ ሁነቶችን እንዲሁም ህዝባዊ ውይይቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጃል ፣ ይደግፋል፤በተደራጀ አግባብ ይመራል ያስተባብራል፤

11. የክልሉን መንግስት ስራዎችና አጠቃላይ ክልላዊና ሀገራዊ ወቅታዊ መረጃዎችን ለክልሉ ህዝብ፣ በሀገርና በውጭ ሀገር ለሚገኙ አካላት ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል የኒው ሚዲያ መስተጋብሮችን አሰራር ይዘረጋል፤አደረጃጀቶችን ይፈጥራል፤  በበላይነት ያስተዳድራል፤ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤

12.የመረጃ አርካይቭና ዶክመቴሽ ስራ ይሰራል፤ የመንግሰት መረጃዎች በአግባቡ እንዲያዙ ያደርጋል ፤ ይቆጣጠራል ፤ የመረጃ ነጻነት አዋጅ እንዲተገበር ያደርጋል፤

13. በክልሉ ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ይሰጣል፤ የሚመለከታቸው ሴክተር መስራያ ቤቶች ተቋሙ በሚያወጣው መርሃ ግብር መሰረት ማብራሪያዎችን እና መግለጫዎችን እንዲሰጡ ያደርጋል፤

14. በክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ውስጥ ያሉ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች በመንግሥት ሠራተኞች ሕግ መሠረት በሜሪት እንዲመደቡ ያደርጋል፤ አፈፃፀሙንም ይከታተላል፤

15.በክልሉ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ክልሉን በሚመለከት የሚወጡ የሚዲያ መረጃዎችን ዳሰሳ በመስራት ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዲሁም እንደ ጉዳዩ ሁኔታ ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፤ ምላሽ እንዲሰጥበት ያድረጋል፤ ከዳሰሳ መረጃዎች በመነሳትም አስፈላጊውን የኮሙዩኒኬሽን ስራ ይሰራል፤

16.ሀገራዊ እና ክልላዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለመረጋገጥ እና የክልሉን ገፅታ ለመገንባት እንዲቻል የተለያዩ የተግባቦት እና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ያከናውናል፤ ለዉጤታማነቱም በክልሉ የሚገኙ ተጽህኖ ፈጣሪ አካላትና ግለሰቦች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ ያስተባብራል፤

17.ልዩ ልዩ የህትመትና የኦዲዮ እና አውዲዮ ቪዝዋል ውጤቶችን ያዘጋጃል፤ በክልሉ  መንግስታዊ ተቋማት የሚከናወኑ የፎቶ ግራፍ፣ የኦዲዮ ቀረፃና የዓርማ እና የህትመት ዲዛይን ተግባራት ፖለቲካዊ፤  ህጋዊ፣ ማህበረሰባዊና የሞራል ጥያቄ የማያስነሱ መሆናቸውን እና ከተቀመጠላቸው ዓላማ ጋር የተገናዘበ መሆኑን ያረጋግጣል፤ አገልግሎት ይሰጣል፤

18.በክልሉ ውስጥ የኮሚዩኒኬሽንና የሚዲያ መሰረተ ልማት የሚጠናከርበትን፣ የሚስፋፋበትን፣ በተገቢው ቴክኖሎጂና ብቃት ባለው የሰለጠነ ባለሙያ የሚደራጅበትን ሥርዓት ይቀይሳል፤ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤

19.የውጪ ማስታወቂያ ስራ ፈቃድ ይሰጣል፤ የውጭ ማስታወቂያ ስራ ለመስራት ለሚፈልጉ ማናቸውም ዜጎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ  ፈቃድ ይሰጣል፤

20.አግባብ ባለው ሕግ ስለውጭ ማስታወቂያ መልካም ሥነ-ምግባር፣ የህብረተሰቡን ማህበራዊና  ባህላዊ እሴቶች የሚያከብር፣ የአገርን እና የክልልን ክብርና ጥቅም የሚያስጠብቅ ይዘትና አቀራረብ ያለው መሆኑን ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤ እርምጃ ይወስዳል ወይም እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡

21.ዓላማዎቹን ከግብ ለማድረስ የሚያስፈልጉ ሌሎች ተዛማጅ ሕጋዊ ተግባራትን ያከናውናል፤