
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉም በክልል ደረጃ “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ የክልል ሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች በፓናል ውይይት አክብረዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መለሰ ኪዊ፣ በክልሉ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል መከበሩ ህገ መንግስቱ ያጎናፀፋቸው መብቶቻቸውን የሚያንፀባርቁበት ነው ብለዋል
ባለፉት ዓመታት የተከበሩት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ አንድነት እና አብሮነታቸው በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ለየት የሚያደርገው ሀገራችን በመፍጠንና በመፍጠር እሳቤ የተጀመሩ በርካታ ፕሮጀክቶች በተጠናቀቁበት ማግስት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርግ ምክትል አፈ-ጉባኤው ገልጸዋል።

በክልሉ የማጠቃለያ መድረክ በካማሽ ዞን ካማሽ ከተማ ላይ ይከበራል ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤው፣ ይህም በዞኑ ያሉትን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለማስተዋወቅና ለማልማት ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሶሳ ዩኒቨርሲት የፌደራልዝም መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አዳሙ ጅባት እንደገለጹት፣ የተለያዩ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ባህሎችን በማክበር የማኅበራዊ ውህደትን በማጎልበት የጋራ መለዮዎችን እና ታሪካዊ እውነታዎችን በማካፈል ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
የእያንዳንዱ ብሔር መብት እና ክብር መከበሩ የሰብዓዊ መብቶች እና እኩልነት ተጠብቀው የተበታተኑ ማህበረሰቦች ድምጻቸውን የሚሰሙበት መድረክ እንደሚፈጥር ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።

