በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመኸር ስንዴ የተገኘውን አበረታች ውጤት በበጋም ለመድገም በትኩረት እየተሰራ ነው፦ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን
****************
(አሶሳ፣ ታህሳስ 24/2016 ዓ.ም) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመኸር ስንዴ የተገኘውን አመርቂ ውጤት በበጋም ለመድገም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።
በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ልዑክ በአሶሳ ዞን አቡራሞ ወረዳ የበጋ ስንዴ የስራ እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የበጋ መስኖ ስንዴ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በክልሉ በ2015/16 የመኸር ወቅት የተገኘውን አበረታች የስንዴ ውጤት በበጋ መስኖ ስንዴም ለመድጋም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።
በክልሉ ስንዴን በስፋት በማልማት ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ባለፉት ጊዜት የተገኙት ውጤቶች ማሣያ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ መንግስት አርሶ አደሩ ከዝናብ ጠባቂነት ወጥቶ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ በመስኖ የለማ የፓፓያ ክላስተርንም ጎብኝተዋል።