“ኢትዮጵያ የባህር ወደብ ባለቤትነት የውል ስምምነት መፈረሟ የፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን የሚያረጋግጥ ነው”። ዶ/ር ተመስገን ዲሳሳ
***** ***** *****
(አሶሳ፣ ታህሳስ 23/2016 ዓ.ም) ኢትዮጵያ የባህር ወደብ ባለቤትነት የውል ስምምነት መፈረሟ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ም/ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ዶ/ር ተመስገን ዲሳሳ ተናገሩ።
ከ30 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነት ስምምነት መፈረሟን አስመልክቶ በአሶሳ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ም/ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ዶ/ር ተመስገን ዲሳሳ፣ኢትዮጵያ በርካታ የውጪ እና የውስጥ ጫናዎችን በመቋቋም የወደብ ባለቤትነት ስምምነት መፈረም መቻሏ የአልበገሬነት መገለጫ ማሳያ ነው ብለዋል።
ይህ ታሪካዊ የመግባቢያ ሰነድ ኢትዮጵያ መፈረሟ ከጎረቤት ሀገረት ጋር ያላትን ጤናማ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ነው ያሉት ዶ/ር ተመስገን የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ የሌላኛውን ጥቅም በማይነካ ፣የደህንነት መውጫ እና የሠላም እና አንድነት መገለጫ መግባቢያ ነው ብለዋል።
የመግባቢያ ሰነዱ የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት እውን የሚያደርግ፣ የባህር በር አማራጮችን የሚያሰፋ፣ የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናከር ነውም ብለዋል
የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም አብዱረሂም በበኩላቸው የከተማው ማህበረሰብ አሁን ያገኘውን ድርብ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም የአብሮነትን እና የአንድነት ባህሉን አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ብለዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይም የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ዶ/ር ተመስገን ዲሳሳ፣የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድርን ጨምሮ የክልል፣የከተማ አስተዳደር፣የዞን እና ወረዳ አመራሮች፣የፀጥታ አካላት ፣መንግስት ሰራተኞች ፣የአሶሳ ከተማ ህዝብ እና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።