የተማሪዎችን ውጤት እና ስነምግባር ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የትምህርቱ ማህበረሰብ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፦ አቶ አሻድሊ ሀሰን

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚደረገው ጥረት የትምህርቱ ማህበረሰብ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

በክልሉ የተማሪዎችን ውጤት እና ስነ-ምግባር ለማሻሻል የሚያስችሉ ክልላዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ተገኝተው የስራ መመሪያ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ ባለፉት ዓመታት በትምህርቱ ዘርፍ ያጋጠሙትን ስብራቶች ለመጠገን በርካታ ተግባራት ተሰርቷል ብለዋል።

በክልሉ በነበረው የፀጥታ ችግር ጫና ውስጥ ከነበሩት ተቋማት የትምህርቱ ዘርፍ አንዱ ነው ያሉት አቶ አሻድሊ ሀሰን፥ የክልሉ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የወደሙ የትምህርት ተቋማትን በመልሶ በማቋቋም የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በክልሉ አብዛኛው የትምህርት ተቋማት ከደረጃ በታች መሆናቸው ለትምህርት ጥራቱ ችግር መሆኑን ገልጸው፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

ወቅቱን የሚጠይቅ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የትምህርት አመራሩ እና ማህበረሰብ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አቶ አሻድሊ አሳስበዋል።

የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተጀመሩ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በማስፋፋት የተማሪዎች ተሳትፎን በማሳደግ ላይ ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በስነ ምግባር የታነፀ ዜጋን ለመፍጠር የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበትም አቶ አሻድሊ አሳስበዋል።

በመድረኩም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የትምህርት ቤት ርዕሳነ-መምህራን የእውቅናና ሰርትፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *