ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በዑራ ወረዳ የማንጎ ክላስተር ሥፍራ ላይ የችግኝ ተከላ አካሄዱ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የተመራ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ልዑክ በዑራ ወረዳ አምባ 5 ቀበሌ በማንጎ ክላስተር ላይ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲሊ ሀሰን፣ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መተግበር ከተጀመረ ወዲህ ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።

በክልሉ የሚተከሉ ችግኞች የታላቁ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ከማገዙም በሻገር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመፍጠር እና የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

የህብረተሰቡ የችግኝ ተከላ ባህል እየተሻሻለ ስለመምጣቱ የጠቆሙት አቶ አሻድሊ፣ የሚተከሉትን ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ እና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው እንደሆኑም ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ ከ7ዐ ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞችን ለመትከል እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ፤ ከሚተከሉት መካከልም አብዛኛው ለምግብነት የሚውሉ ናቸው ብለዋል።

የህብረተሰቡ የችግኝ ተከላ ባህል እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ጠቁመው፣ የለመለመች እና የበለፀገች ሀገርን ለትውልድ ማስተላለፍ የሚቻለው ዛሬ የሚተከሉ ችግኞችን መንከባከብ ስንችል ብቻ ነው ብለዋል።

የሚተከሉትን ችግኞች ከሰው እና ከእንስሳት ንኪኪ ነፃ በማድረግ በአግባቡ እንክብካቤ ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *