በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል፦ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን::

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የፓርቲውን አባላት እና መላው ህዝቡን በማሳተፍ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አባላት ክልላዊ ማጠቃለያ ኮንፍረንስ “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻደሊ ሀሰን፣ ባለፉት የለውጥ ጊዜያት የክልሉ መንግስት በፈተናዎች ውስጥ ሆኖ አበረታች ለውጦች ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የተፈፀሙ ጉልህ ተግባራት እና ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆኖ ባለፉት የሁለት ዓመት ተኩል የምርጫ ዘመን መላውን የብልፅግና ፓርቲ አባላት እና ህዝቡን በማሳተፍ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪዎች ናቸው ብለዋል፡፡

በተለይም በክልሉ በግብርና እና በአምራች ኢንዱስትሪው፣ በማዕድን እና በቱሪዝም ሀብት ልማት በአርንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር፣ በክረምት በጎ አገልግሎት ስራዎች፣ በጤና፣ በትምህርት እና በንፁህ መጠጥ ውሃ የተመዘገቡ ውጤቶች ማሳያ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

የክልሉን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ከማሟላት የንግዱን ማህበረሰብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ የንግድ ስርዓቱን ለማዘመንና ህጋዊ ስርዓቱን እንዲይዝ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

የሴቶችን እና ወጣቶችን በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው ያሉት፡፡

በክልሉ የትምህርት ጥራት ጉድለት፣የመድሃኒት አቅርቦት እና ስርጭት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተባበረ ክንድ መቅረፍ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድር አሻዲሊ ሀሰን ፤አሁን በክልሉ የተገኘውን አንፃራዊ ሠላም መላው ህዝብ መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር፤የክልሉን ህዝብ ሠላም እና ደህኒነት ማስጠበቅ፣የመልካም አስተዳድር ጥያቄዎችን መፍታት፣የህዝቦችን የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እና ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትን በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆም በቀሪ ጊዜያቶች በትኩረት እንደሚሰራበት ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *