************
መገናኛ ብዙሃን ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።
ከተለያዩ የግል መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለአራት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ተገኝተዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙሃን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ሥርዓት ግንባታ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
ሀገራዊ መግባባት ላይ መገናኛ ብዙሃን በሚጠበቀው ደረጃ እየሰሩ እንዳልሆነ ገልጸው ሕዝቡን የሚያቀራርቡ እንድነትን የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ ሚዛናዊ ሆኖ ከመዘገብ ይልቅ ወገንተኝነት እየተስተዋለ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ይህም ለሰላም እና ሀገር ግንባታ ሳንካ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መገናኛ ብዙሃን በስራዎቻቸው ሀገርን ማስቀደም እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ መንግስት አስፈላጊውን ደጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
በመድረኩ የውይይት መነሻ ያቀረቡት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን አብሮ የሚያኖር ነገር እየሰራን ነው ወይ?፣ ትውልድ እየገነባን ነው ወይ የሚለውን ቆም ብለው ሊያጤኑት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አቅም ማነስ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ እንዲሁም የግንዛቤ ክፍተቶች በአግባቡ እንዳይሰሩ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች መካከል ይገኝበታል።
በቀጣይም መገናኛ ብዙሃን የሕግና ሙያዊ ሥነ ምግባር ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ስልጠናዎች መስጠት እንዲሁም ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ መተግበር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የአዋሽ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኛ አህመድ አደም የግል መገናኛ ብዙሃን ገቢ በሚያስገኙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው በብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ መግባባት ዙሪያ ትኩረት አድርገው እንዳይሰሩ ማድረጉን ነው የተናገረው፡፡
መገናኛ ብዙሃን በተለይ ማህበረሰብን ማስተማርና ማንቃት ላይ ትኩረት ማድረግ አንዳለባቸውም ነው የተናገረው፡፡
ከአራዳ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ የመጣው ጋዜጠኛ ዳዊት በሪሁን በበኩሉ በአንዳንድ መረጃ ሰጪዎች ዘንድ የሚስተዋለው መረጃ ያለመስጠት ችግር መገናኛ ብዙሃን በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሰሩ እክል መፍጠሩን ነው ያነሳው፡፡
ማህበራዊ ሚዲያው እየፈጠረ ያለው አሉታዊ ጫና ቸል ሊባል እንደማይገባ የተናገረው ደግሞ የአዲስ ዋልታ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሳሙኤል ዳኛቸው ነው።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ መረጃዎችን በተገቢው መልኩ ማጥራት እንደሚገባም ነው የተናገረው፡፡
ኢዜአ