የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ከካማሽ ስፖርት ምክር ቤት ጋር በመተባበር የማህበረሰብ አቀፍ የጤናና የአካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ንቅናቄ ማስጀመሪያ በካማሽ ዞን ካማሽ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል ።
በማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተገኙት የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዩሱፍ አልበሽር፣ “ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል አምራቹ የህብረተሰብ ክፍል የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትሮ በመስራት ጤናውን ሊጠብቅ ይገባል” ብለዋል።
በዞኑ የተካሄደው የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን መካሄዱ ከዞኑ የተገኘችው ድንቅና ብርቅየዋ አትሌት ጽጌ ዱጉማ በግላስኮ ስኮትላንድ የ800 ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሀገራችን ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት የሀገራችንን፣ የክልላችንና የካማሽ ዞንን መንግስትና ህዝብን ባኮራችበት ማግስት ላይ መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው ገልዋል።
የካማሽ ከተማ ከንቲባ ኢንጅነር አብደታ ደሬሳ፣ ማኅበረሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለውን ጥቅም በውል በመረዳት አዘውትሮ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል ።
አትሌት ጽጌ ድጉማ ከካማሽ ዞን የተገኘች ድንቅና ብርቅየዋ ልጃቸው በአለም መድረክ የወርቅ ሜዳልያ በማምጣት ሀገራችንን ኢትዮጵያን ማስጠራት በመቻሏ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ፣ በዞኑ በርካታ ተተኪ ጽጌዎችን ለማፍራት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የካማሽ ዞን ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚችል እምቅ አቅም ያለው በክልላችን ትኩረት የሚደረግበት ዞን ሲሆን የክልሉ ስፖርት ኮሚሽንም ትኩረት አድርጎ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በአካል ብቃት እንቅስቃሴው የካማሽ ዞን፣ የካማሽ ከተማ አስተዳደርና የወረዳ አመራሮች፣ የካማሽ ከተማ ማህበረሰብ፣ስፖርተኞች ፣ ነጋዴዎች ፣ተማሪዎች፣ ባለሙያዎችና የስፖርት አማተር አገልጋዮች መሳተፋቸው ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።