በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የትምህርት ቤት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ለማከናወን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
የክልሉ ካቢኔ በሠላም ሚኒስቴር ድጋፍ እና በክልሉ መንግሥት በጀት እየተከናወኑ በሚገኙ የትምህርት ቤት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ የዲዛይን ማሻሻያ እና ጥራት ዙሪያ ተወያይቷል።
በውይይቱም በክልሉ በኢፌዴሪ ሠላም ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ እና በክልሉ መንግሥት በጀት እየተከናወኑ የሚገኙ እና ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ 9 የትምህርት ቤት ፕሮጀክቶች መኖራቸው ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይም የትምህርት ቤት ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
በሠላም ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ እና በክልሉ መንግሥት በጀት እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የትምህርት ቤት ግንባታዎች በወቅቱ ለማጠናቀቅ፣ ዲዛይናቸውን አሁን ካለው ወቅታዊ የገበያ ሁኔታ እና የመንግሥት በጀት አቅም ጋር ማጣጣም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የፕሮጀክቶቹ መጓተት መንግሥትን ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ ነው ያሉት አቶ አሻድሊ፣ በሠላም ሚኒስቴር ድጋፍም ይሁን በክልሉ መንግሥት በጀት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ጠብቀው በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊው የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጎላቸው በወቅቱ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻዎች ርብርብ አስፈላጊ መሆኑንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የጠቀሱት።
ግንባታዎቹን ለማጠናቀቅ በክልሉ ትምህርት ቢሮ እና በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ተዘጋጅቶ በቀረበው የዲዛይን ማሻሻያ ላይ የተወያዬው ካቢኔው፣ በማሻሻው መሠረት ወደሥራ እንዲገባም አቅጣጫ አስቀምጧል።
ካቢኔው የበጀት አመቱ የ6 ወራት አፈፃጸም ሪፖርት ላይ በመወያየት በግማሽ አመቱ የተሰሩ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠልና የታዩ ክፍተቶችን በማረምና ቀሪ ስራዎችን ያለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ መፈጸም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ሪፖርቱን አጽድቋል፡፡