የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ከተለያዩ ወረዳዎች የተሰበሰቡ ከዓድዋ ድል ጋር የተያያዙ የተለያዩ ቅርሶችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስረከበ።
ከዓድዋ ድል ጋር የተያያዙ ቅርሶች በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የሚደራጁ ቅርሶችን በማሰባሰብ እንዲደራጅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ባደረገው ጥሪ መሰረት ከተለያዩ ወረዳዎች የተሰበሰቡ የተለያዩ ከድሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ቅርሶችን ለከተማ አስተዳደሩ በዛሬው ዕለት አስረክበዋል።
ቅርሶቹን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ምስኪያ አብደላ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስረክበዋል።
በከተማ አስተዳድሩ የከንቲባ ጽ/ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ የከተማ አስተዳደሩ ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ከተለያዩ ወረዳዎች ያሰባሰባቸውን ከዓድዋ ድል ጋር የተያያዙ ቅርሶችን በማበርከቱ በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
መሰል ከዓድዋ ድል ጋር የተያያዙ ቅርሶች ትውልድ እንዲማርባቸው በመታሰቢያ ሙዚየም ውስጥ ለማስቀመጥ እየሠራ መሆኑን መግለጻቸውን ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

