የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማካሄድ ጀመረ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወከሉ ተመራጮች እና ከባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ ውይይት ማካሄድ ጀምሯል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ በክልሉ ከሶስቱም ዞኖች፣ ከ27 ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 200 በላይ የህብረተሰብ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘገዬ አስፋው፣ ኮሚሽኑ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመው፣ ለአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚወከሉ የህብረተሰብ ተወካዮችን ከየክልሎቹ ልየታ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት መጀመሩን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ስድስት ቀናት የሚቆይ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መጀመሩን ተናግረዋል።

ኮሚሽሽኑ እያከናወነ ያለው የምከክር ሂደት የሁሉም ድምጽ የሚሰማበትንና የመፍትሔ አማራጮች የሚቀመጡበትን ያስቀደመ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ይህም ሠላምን ዘለቂ በማረጋገጥ ለሀገሪቱ መጻኢ ዕድል ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የተገኙ ወካይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የመንግስት አካላት፣ የተለያዩ ተቋማት ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተወያይተው፣ የአጀንዳ ሃሳባቸውን እንደሚያዘጋጁ እና እንደሚያቀርቡም ይጠበቃል።